የተፍሲር ክፍል

መልስ- ሱረቱ አል'ፋቲሓ እና ተፍሲሩ፡-
{"ቢስሚላሂ-ር-ሯሕማኒ-ር-ሯሒም" "በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።"(1) «አልሓምዱ ሊልላሂ ረቢል ዓለሚን» (ምስጋና ለዓለማት ጌታ ለአላህ የተገባው ነው) (2) "አር-ሯሕማኒ-ር-ሯሒም" "እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ ለሆነው።"(3) «ማሊኪ የውሚ‐ድ‐ዲን» (ትርጉሙም: የፍርዱ ቀን ባለቤት) (4) «ኢይ-ያከ ነዕቡዱ ወኢይያከ ነሰተዒን» (አንተን ብቻ እንገዛለን አንተንም ብቻ እርዳታን እንለምንሃለን) (5) «ኢህዲና‐ስ‐ሲሯጦል ሙስተቂም» (ትርጉሙም: ቀጥተኛውን መንገድ ምራን) (6) «ሲሯጦ‐ል‐ለዚነ አንዓምተ ዓለይሂም ቐይሪል መቕዱቢ ዓለይሂም ወለድዷሊን» (ትርጉሙም: የእነዚያ ፀጋህን የዋልክላቸውን ሰዎች መንገድ በነዚያ የተቆጣህባቸውን እና የተሳሳቱትንም አይደሉም። 7} [ሱረትይ አል'ፋቲሓ፡ 1 - 7]
ተፍሲር፡
ሱረቱል ፋቲሓ (የመክፈቻዋ ሱራ)
የተባለችበት ምክንያት የአላህ ኪታብ የሚጀረው በእርሷ ስለሆነው ነው።
{"በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።"} ቁርኣንን መቅራቴን በአላህ ስም እጀምራለሁ፤ በላቀው አላህ እታገዝ ዘንድ ስሙን በማውሳት በረካውንም እንዳገኝ።
{አላህ} ማለት በእውነት የሚመለከው ብቸኛ ማለት ሲሆን ይህ ስያሜ ጥራት ይገባውና ከእርሱ ውጭ ማንም የሚጠራበት አይደለም።
{አር-ረሕማን} ማለትም ሁሉንም ያካለለ የሰፊ እዝነት ባለቤት ነው።
{አር-ረሒም} ማለትም ለምእመናኑ ልዩ እዝነት ያለው ነው።
2- {"ምስጋና ለዓለማት ጌታ ለአላህ የተገባው ነው"} ማለትም የውዳሴናም የፍፁምነትም ዓይነቶች ሁሉ ለአላህ ብቻ የተገባ ነው።
3- {"እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ ለሆነው።"} ማለትም ሁሉንም ነገር ያካለለ ሰፊ እዝነት ባለቤት እና ለምእመናን በልዩ ሁኔታ የሚደርስ የልዩ እዝነት ባለቤት ነው።
4- {"የፍርዱ ቀን ባለቤት"} ማለትም የምጽአት ቀን ባለቤቱ እርሱ ነው።
5- ("አንተን ብቻ እንገዛለን አንተንም ብቻ እርዳታን እንለምንሃለን") ማለትም ካንተ ውጭ ሌላን ሳናመልክ በብቸኝነት እናመክልሃለን ፤ አንተን ብቻ እገዛ እንጠይቅሃለን።
6- {"ቀጥተኛውን መንገድ ምራን"} ማለትም ለእስልምና እና ለሱና መገጠም ነው።
7- {"የእነዚያ ፀጋህን የዋልክላቸውን ሰዎች መንገድ በነዚያ የተቆጣህባቸውን እና የተሳሳቱትንም አይደሉም።"} ማለትም የክርስቲያኖችንና የአይሁዶችን መንገድ ሳይሆን የነብያትና የአላህ ደጋግ ባሮች መንገድ ምራን ማለት ነው።
ይህንን ከቀሩ በኋላ “አሚን” ማለቱ ሱና ነው። ማለትም የሚወደድ ነው።

መልስ- ሱረቱል ዘልዘላህ እና ተፍሲሩ
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{ምድር (በኀይል) መንቀጥቀጥዋን በተንቀጠቀጠች ጊዜ፤ 1 * ምድር ሸክሞችዋን ባወጣችም ጊዜ፤ 2 * ሰውም ምን ሆነች? ባለ ጊዜ፤ 3 * በዚያ ቀን ወሬዎችዋን ትናገራለች። 4 * ጌታህ ለእርሷ በማሳወቁ ምክንያት። 5 * በዚያ ቀን ሰዎች ሥራዎቻቸውን (ምንዳዋን) እንዲያዩ ይደረጉ ዘንድ (እንደየሥራቸው) የተለያዩ ሆነው (ከመቆሚያው ስፍራ) ይመለሳሉ። 6 * የብናኝ ክብደት ያክልም መልካምን የሠራ ሰው ያገኘዋል። 7 * የብናኝ ክብደት ያክልም ክፉን የሠራ ሰው ያገኘዋል። 8} [ሱረቱ-ዘልዘላህ፡ 1-8]
ተፍሲር፡
1- {ምድር (በኀይል) መንቀጥቀጥዋን በተንቀጠቀጠች ጊዜ፤ 1} ማለትም በዕለተ ትንሳኤ ከሚደርስባት ከባድ እንቅስቃሴ አንፃር ምድር በተንቀጠቀጠች ጊዜ።
2- {"ምድር ሸክሞችዋን ባወጣችም ጊዜ፤ 2"} ማለትም ምድር በሆዷ ውስጥ ያለውን ሙታንም ሌላውንም ባወጣች ጊዜ።
3- {"ሰውም ምን ሆነች? ባለ ጊዜ፤ 3"} የሰው ልጅ ግራ ተጋብቶ "ምድር ምን ነክቷት ነው የምትንቀጠቀጠውና የምትናወጠው?!" ይላል።
4- {"በዚያ ቀን ወሬዎችዋን ትናገራለች። 4"} በዚያ ከባድ ቀን ምድር እርሷ ላይ የተደረገውን መልካምና ክፉውን ሁሉ ምድሪቱ ትዘከዝከዋለች።
5- {"ጌታህ ለእርሷ በማሳወቁ ምክንያት። 5"} ምክንያቱም አላህ ስላሳወቃትና እንድትናገርም ስላዘዛት ነው።
6- {"በዚያ ቀን ሰዎች ሥራዎቻቸውን (ምንዳዋን) እንዲያዩ ይደረጉ ዘንድ (እንደየሥራቸው) የተለያዩ ሆነው (ከመቆሚያው ስፍራ) ይመለሳሉ። 6"} በዚያ ምድሪቱ በምትናወጥበት ከባድ ቀን ሰዎች በዱኒያ ሳሉ የሰሩትን ሊመለከቱ ቡድን ቡድን እየሆኑ ወደ መተሳሰቢያው መስክ ይወጣሉ።
7- {"የብናኝ ክብደት ያክልም መልካምን የሠራ ሰው ያገኘዋል። 7"} በመሆኑም የትንሿን ትንኝ ክብደት ያህል እንኳ በጎ የሰራ ሰው ስራውን ፊት ለፊቱ ሆኖ ይመለከተዋል።
8- {"የብናኝ ክብደት ያክልም ክፉን የሠራ ሰው ያገኘዋል። 8"} በሷው ክብደት ልክ ክፉ ሥራ የሠራም ሰው እንዲሁ ስራውን ፊት ለፊቱ ሆኖ ይመለከተዋል።

መልስ- ሱረቱ አል'ዓዲያት እና ተፍሲሯ፡-
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{እያለከለኩ ሯጮች በሆኑት (ፈረሶች) እምላለሁ። 1 * (በሰኮናቸው) እያጋጩ እሳትን አውጪዎች በሆኑትም፤ 2 * በማለዳ ወራሪዎች በሆኑትም፤ 3 * በእርሱ አቧራን በቀሰቀሱትም፤ 4 * በ(ጠላት) ክቢ መካከል በእርሱ (በጧት) በተጋፈጡትም እምላለሁ። 5 * ሰው ለጌታው ብርቱ ከሓዲ ነው። 6 * እርሱም በዚህ ላይ መስካሪ ነው። 7 * እርሱም ገንዘብን ለመውደድ በጣም ብርቱ ነው። 8 * (ሰው) አያውቅምን? በመቃብሮች ያሉት (ሙታን) በተቀሰቀሱ ጊዜ፤ 9 * በልቦች ውስጥ ያለውም ሁሉ በተገለጸ ጊዜ (እንዴት እንደሚሆን)። 10 * ጌታቸው በዚያ ቀን በእነርሱ (ነገር) በእርግጥ ውስጠ አዋቂ ነው። 11} [ሱረቱ አል'ዓዲያት: 1-11]
ተፍሲር፡
1- {"እያለከለኩ ሯጮች በሆኑት (ፈረሶች) እምላለሁ። 1"} አላህ ከሩጫ ብዛት የሚያለከልኩት ድምጽ በሚሰማ በሆኑ ፈረሶች ማለ።
2- {"(በሰኮናቸው) እያጋጩ እሳትን አውጪዎች በሆኑትም፤ 2"} ቋጥኞችን በኋይለኛው በመምታታቸው ምክንያት በቋጥኙ ላይ ከሚያደርሱት ተጽእኖ አንፃር እሳትን በሚለኩሱ ፈረሶችም ማለ።
3- {"በማለዳ ወራሪዎች በሆኑትም፤ 3"} በማለዳው ጠላት ላይ የሚበረቱ በሆኑ ፈረሶችም ማለ።
4- {"በእርሱ አቧራን በቀሰቀሱትም፤ 4"} በሩጫቸው አቧራ የሚቀሰቅሱ በሆኑትም ማለ።
5- {"በ(ጠላት) ክቢ መካከል በእርሱ (በጧት) በተጋፈጡትም እምላለሁ። 5"} ፈረሰኞቻቸውም በርካታ በሆኑ ጠላቶች መካከል የሚሰርጉባቸው በሆኑ ማለ።
6- {"ሰው ለጌታው ብርቱ ከሓዲ ነው። 6
"}
ሰውም ጌታው ከርሱ የሚፈልገውን ደግ ነገር ከማድረግ ይነፍጋል።
7- {"እርሱም በዚህ ላይ መስካሪ ነው። 7
"}
መልካምን የሚከለክል መሆኑ ግልጽ በመሆኑ የማይክደው የሚመሰክረው ጉዳይ ነው።
8- {"እርሱም ገንዘብን ለመውደድ በጣም ብርቱ ነው። 8
"}
ለገንዘብም ድንበር ያለፈ ውዴታ ያለው በመሆኑም ንፉግ ነው።
9- {"(ሰው) አያውቅምን? በመቃብሮች ያሉት (ሙታን) በተቀሰቀሱ ጊዜ፤ 9"} ይህ በቅርቢቱ ሕይወት የተታለለ ሰው አላህ በመቃብር ውስጥ ያሉትን ሙታንን አስነስቶ ለመተሳሰብና ለፍርድም ከምድር በሚያስወጣቸው ጊዜ ነገሩ እንዳሰበው እንዳልሆነ አያውቅምን?!
10- {"በልቦች ውስጥ ያለውም ሁሉ በተገለጸ ጊዜ (እንዴት እንደሚሆን)። 10"} ከሀሳብም ከእምነትም አኳያ በልቦች ውስጥ ያለውም ሌላውም ነገር ጎልቶና ግልፅ ሆኖ ይወጣል።
11- {"ጌታቸው በዚያ ቀን በእነርሱ (ነገር) በእርግጥ ውስጠ አዋቂ ነው። 11"} ጌታቸው በዚያ ቀን በነርሱ ላይ ዐዋቂ ነው። ከባሮቹ ምንም ነገር የማይደበቅበትና ለነርሱም በስራቸው ምንዳቸውን የሚከፍላቸው ነው።

መልስ- ሱረቱ አል'ቃሪዓህ እና ተፍሲሩ:
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{ቆርቋሪይቱ (ጩኸት)፤ 1 * ምን አስደናቂ ቆርቋሪ ናት! 2 * ቆርቋሪይቱም ምን እንደሆነች ምን አሳወቀህ? 3 * ሰዎች እንደ ተበታተነ ቢራቢሮ (ወይም ኩብኩባ) በሚሆኑበት ቀን፤ 4 * ጋራዎችም እንደ ተነደፈ ሱፍ በሚሆኑበት (ቀን ልቦችን በድንጋጤ ትቆረቁራለች።) 5 * ሚዛኖቹ የከበዱለት ሰውማ፤ 6 * እርሱ በምትወደድ ኑሮ ውስጥ ይሆናል። 7 * ሚዛኖቹም የቀለሉበት ሰውማ፤ 8 * መኖሪያው ሃዊያህ ናት፤ 9 * እርሷም ምን እንደ ሆነች ምን አሳወቀህ? 10 * (እርሷ) በጣም ተኳሳ እሳት ናት።} [ሱረቱል አል'ቃሪዓህ 1-11]
ተፍሲር፡
1- {"{ቆርቋሪይቱ (ጩኸት)፤ 1"} ከአስፈሪነቷ አንፃር የሰዎችን ልብ የምታንኳኳ የሆነችው ሰዓት።
2- {"ምን አስደናቂ ቆርቋሪ ናት! 2"} ከአስፈሪነቷ አንፃር የሰዎችን ልብ የምታንኳኳ የሆነችው ሰዓት ምንድን ነች?!
3- {"ቆርቋሪይቱም ምን እንደሆነች ምን አሳወቀህ? 3"} መልእክተኛ ሆይ! ከአስፈሪነቷ አንፃር የሰዎችን ልብ የምታንኳኳ የሆነችው ሰዓት ምንነት ምን የምታውቀው አለ?! እርሷ`ማ የቂያም ቀን ነች።
4- {"ሰዎች እንደ ተበታተነ ቢራቢሮ (ወይም ኩብኩባ) በሚኾኑበት ቀን፤ 4"} ሰዎች ልባቸው በሚቆረቆርበት ቀን እዚህም እዚያም ተበታትነው እንደተበተነ ቢራቢሮ (ወይም ኩብኩባ) ይሆናሉ።
5- {"ጋራዎችም እንደ ተነደፈ ሱፍ በሚሆኑበት (ቀን ልቦችን በድንጋጤ ትቆረቁራለች።) 5"} ተራሮችም ከእንቅስቃሴያቸው ቀላልነት አንፃር እንደ ክፍት ሱፍ ይሆናሉ።
6- {"ሚዛኖቹ የከበዱለት ሰውማ፤ 6"} መልካም ስራው ከመጥፎ ስራው የሚበልጥ የሆነለት ሰው`ማ።
7- {"እርሱ በምትወደድ ኑሮ ውስጥ ይሆናል። 7"} ጀነት ውስጥ በተጎናፀፈው አጥጋቢ ህይወት ላይ ነው።
8- {"ሚዛኖቹም የቀለሉበት ሰውማ፤ 8"} መጥፎ ስራው ከመልካም ስራው የሚበልጥ የሆነበት ሰው`ማ።
9- {"መኖሪያው ሃዊያህ ናት፤ 9"} በእለተ ትንሳኤ መኖሪያ እና ማረፊያው ጀሀነም ነው።
10- {"እርሷም ምን እንደ ሆነች ምን አሳወቀህ? 10"} አንተ መልእክተኛ ሆይ! - ምን እንደሆነች ምን አሳወቀህ?!
11- {"(እርሷ) በጣም ተኳሳ እሳት ናት።"} እርሷ ትኩሳቷ የበረታ እሳት ነች።

መልስ- ሱረቱ ተካሡር እና ተፍሲሩ፦
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{በብዛት መፎካከር (ጌታችሁን ከመገዛት) አዘነጋችሁ። 1 * መቃብሮችን እስከ ጎበኛችሁ ድረስ። 2 * ተከልከሉ፤ ወደፊት (ውጤቱን) ታውቃላችሁ። 3 * ከዚያም ተከልከሉ፤ ወደ ፊት ታውቃላችሁ። 4 * በእውነቱ (የሚጠብቃችሁን) እርግጠኛ ዕውቀትን ብታውቁ ኖሮ፤ (ባልዘናጋችሁ ነበር)። 5 * ገሀነምን በርግጥ ታያላችሁ። 6 * ከዚያም እርግጠኛን ማየት ታዩዋታላችሁ። 7 * ከዚያም ከድሎታችሁ ሁሉ በዚያ ቀን ትጠየቃላችሁ። 8} [ሱረቱ ተካሡር: 1-8]
ተፍሲር፡
1- {"{በብዛት መፎካከር (ጌታችሁን ከመገዛት) አዘነጋችሁ። 1"} ሰዎች ሆይ! በገንዘብና በልጆች መፎካከራችሁ አላህን ከመገዛት አዘነጋችሁ።
2- {"መቃብሮችን እስከ ጎበኛችሁ ድረስ። 2"} ሞታችሁ ወደ መቃብራችሁ እስክትገቡ ድረስ አዘነጋችሁ።
3- {"ተከልከሉ፤ ወደፊት (ውጤቱን) ታውቃላችሁ። 3"} በእርሷ መፎካከራችሁ አላህን ከመታዘዝ ሊያዘናጋችሁ የሚገባ አይደለም። የዚህ መዘናጋታችሁ መጨረሻውን ታዩታላችሁ።
4- {"ከዚያም ተከልከሉ፤ ወደ ፊት ታውቃላችሁ። 4"} አሁንም ፍፃሜውን ታውቃላችሁ።
5- {"በእውነቱ (የሚጠብቃችሁን) እርግጠኛ ዕውቀትን ብታውቁ ኖሮ፤ (ባልዘናጋችሁ ነበር)። 5"} በእርግጥ ወደ አላህ ተመላሾች መሆናችሁንና በሥራችሁንም እንደሚመነዳችሁ በእርግጠኝነት ብታውቁ ኖሮ በገንዘብና በልጆች መፎካከር ላይ አትጠመዱም ነበር።
6- {"ገሀነምን በርግጥ ታያላችሁ። 6"} በመሀላ አስረግጨ እናገራለሁ በእለተ ትንሣኤ እሳትን ትመለከታላችሁ።
7- {"ከዚያም እርግጠኛን ማየት ታዩዋታላችሁ። 7"} ከዚያም ያለምንም ጥርጥር በተጨባጭ ትመለከቷታላችሁ።
8- {"ከዚያም ከድሎታችሁ ሁሉ በዚያ ቀን ትጠየቃላችሁ። 8"} ከዚያም አላህ በዚያን ቀን ከጤናም ከሀብትም ከሌሎችም ፀጋዎች በኩል ስለዋለላችሁ ውለታ ይጠይቃችኋል።

መልስ - ሱረቱል ዐስር እና ተፍሲሯ፦
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{በጊዚያቱ እምላለሁ፤ 1 * ሰው ሁሉ በእርግጥ በከሳራ ውስጥ ነው። 2 * እነዚያ ያመኑትና መልካሞችን የሠሩት፣ በእውነትም አደራ የተባባሉት፣ በመታገስም አደራ የተባባሉት ብቻ ሲቀሩ። 3} [ሱረቱል ዐስር: 1-3]
ተፍሲር፡
1- {በጊዚያቱ እምላለሁ፤ 1} ጥራት ይገባውና በጊዜያቱ ማለ።
2- {ሰው ሁሉ በእርግጥ በከሳራ ውስጥ ነው። 2} ማለትም፡- የሰው ልጆች ሁሉ በውድቀት እና በጥፋት ላይ ናቸው።
3- {እነዚያ ያመኑትና መልካሞችን የሠሩት፣ በእውነትም አደራ የተባባሉት፣ በመታገስም አደራ የተባባሉት ብቻ ሲቀሩ። 3} እነዚያ አማኝ ሆነው መልካም ሥራዎችንም የሠሩት፤ ወደ እውነትም የተጣሩ በርሱም ላይ የታገሡት ከኪሳራ የዳኑ ናቸው።

መልስ - ሱረቱል ሁመዛህ እና ተፍሲሯ፦
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{ለሃሜተኛ ለዘላፊ ሁሉ ወዮለት። 1 * ለዚያ ገንዘብን የሰበሰበና የቆጣጠረው (ያደለበውም) ለሆነ ፤(ወዮለት)። 2 * ገንዘቡ የሚያዘወትረው መሆኑን ያስባል። 3 * ይከልከል፤ በሰባሪይቱ (እሳት) ውስጥ በእርግጥ ይጣላል። 4 * ሰባሪይቱም ምን እንደ ሆነች ምን አሳወቀህ? 5 * የተነደደችው የአላህ እሳት ናት። 6 * ያቺ በልቦች ላይ የምትዘልቅ የሆነችው። 7 * እርሷ በእርግጥ በእነርሱ ላይ የተዘጋጀች ናት። 8 * በተዘረጋች አዕማድ ውስጥ (የተዘጋች ናት)። 9 [ሱረቱ አል-ሁመዛህ: 1-9]
ተፍሲር፡
1- {ለሃሜተኛ ለዘላፊ ሁሉ ወዮለት። 1} ሰዎችን አብዝቶ ለሚያማ እና ለሚዘልፍ ሰው የመከራ እና የስቃይ ቅጣት አለበት።
2- {ለዚያ ገንዘብን የሰበሰበና የቆጣጠረው (ያደለበውም) ለሆነ ፤(ወዮለት)። 2} ለዛ ገንዘብ ከመሰብሰብና ከመቁጠር ውጭ ሌላ ሀሳብ ለሌለው ወዮለት።
3- {ገንዘቡ የሚያዘወትረው መሆኑን ያስባል። 3} የሰበሰበው ገንዘብ ከሞት ያድነዉና በዱንያ ህይወትም የሚያዘወትረው ይመስለዋል።
4- {ይከልከል፤ በሰባሪይቱ (እሳት) ውስጥ በእርግጥ ይጣላል። 4} ጉዳዩ ይህ አላዋቂ እንዳሰበው አይደለም። ይልቁን ከከባድነቷ አንፃር የተወረወረላትን ሁሉ የምትፈጭና የምትሰባብር ወደሆነችው የጀሀነም እሳት ይወረወራል።
5- {ሰባሪይቱም ምን እንደ ሆነች ምን አሳወቀህ? 5} የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ይህች የተጣለላትን ሁሉ የምትፈጨው እሳት ምንነት ምን አሳወቀህ?!
6- {የተነደደችው የአላህ እሳት ናት። 6} እርሷ የምትቀጣጠል የአላህ እሳት ነች።
7- {ያቺ በልቦች ላይ የምትዘልቅ የሆነችው። 7} በሰዎች አካል ወደ ልባቸው ዘልቃ የምትገባ ነች።
8- {እርሷ በእርግጥ በእነርሱ ላይ የተዘጋጀች ናት። 8} በውስጧ ለሚሰቃዩባትም የምትቆለፍባቸው ነች።
9- {በተዘረጋች አዕማድ ውስጥ (የተዘጋች ናት)። 9} ከውስጧም እንዳይወጡ በተዘረጉ ረዣዥም አዕማድ የተዘጋች ነች።

መልስ - ሱረቱል ፊል እና ተፍሲሯ፦
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{በዝሆኑ ባለቤቶች ጌታህ እንዴት እንደሠራ አላወቅህምን? 1 * ተንኮላቸውን በጥፋት ውስጥ (ከንቱ) አላደረገምን? (አድርጓል)። 2 * በእነርሱም ላይ መንጎች የሆኑን ዎፎች ላከ። 3 * ከተጠበሰ ጭቃ በሆነ ድንጋይ የምትወረውርባቸው የሆነችን፤ (አዕዋፍ)። 4 * ቅጠሉ እንደ ተበላ አዝመራም አደረጋቸው። 5} [ሱረቱል ፊል: 1-5]
ተፍሲር፡
1- {በዝሆኑ ባለቤቶች ጌታህ እንዴት እንደሠራ አላወቅህምን? 1} አንተ የአላህ መልእክተኛው ሆይ! እነዚያ የዝሆን ባለቤቶች የሆኑት አብርሃና ባልደረቦቹ ካዕባን ለማውደም በፈለጉ ጊዜ ጌታህ እንዴት እንዳደረጋቸው አታውቅምን?!
2- {ተንኮላቸውን በጥፋት ውስጥ (ከንቱ) አላደረገምን? (አድርጓል)። 2} ለማውደም ያቀዱበትን መጥፎ ጥንስሳቸውን ከንቱ አደረገባቸው። ሰዎችን ከካዕባ ከማዘናጋት አንፃር የፈለጉትንም አላገኙ፤ ከተንኮላቸው አንዳች ነገርንም አላተረፉም።
3- {በእነርሱም ላይ መንጎች የኾኑን ዎፎች ላከ። 3} በእነርሱም ላይ አእዋፍን በቡድን በቡድን አድርጎ ላከባቸው።
4- {ከተጠበሰ ጭቃ በሆነ ድንጋይ የምትወረውርባቸው የኾነችን፤ (አዕዋፍ)። 4} ከተጠበሰ ሸክላ የሆነን ድንጋይ ትወረውርባቸዋለች።
5- {ቅጠሉ እንደ ተበላ አዝመራም አደረጋቸው። 5} አላህም በእንስሳት ተበልቶ እንደተጣለ ቅጠል አደረጋቸው።

መልስ- ሱረቱ ቁረይሽ እና ተፍሲሯ፦
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{ቁረይሾችን ለማላመድ(ባለዝሆኖቹን አጠፋ)። 1 * የብርድና የበጋን ወራት ጉዞ ሊያላምዳቸው ይህንን ሠራ። 2 * ስለዚህ የዚህን ቤት (የከዕባን) ጌታ ይግገዙ። 3 * ያንን ከረኃብ ያበላቸውን ከፍርሃትም ያረካቸውን (ጌታ ያምልኩ)። 4} (ሱረቱ ቁረይሽ፡ 1-4)
ተፍሲር፡
1- {ቁረይሾችን ለማላመድ (ባለዝሆኖቹን አጠፋ)። 1} በክረምት እና በበጋ ወቅት የለመዱትን ጉዞ የተመለከተ ነው።
2- {የብርድና የበጋን ወራት ጉዞ ሊያላምዳቸው ይህንን ሠራ። 2} በክረምት ወደ የመን እና በበጋ ደግሞ ወደ ሻም የሚያደርጉት ጉዞ ነው።
3- {ስለዚህ የዚህን ቤት (የከዕባን) ጌታ ይግገዙ። 3} የዚህ የተቀደሰ ቤት ጌታ የሆነውን እና ይህንንም ጉዞ ያገራላቸውን አላህን በርሱም ምንንም ሳያጋሩ እርሱን ብቻ ያምልኩ።
4- {ያንን ከረኃብ ያበላቸውን ከፍርሃትም ያረካቸውን (ጌታ ያምልኩ)። 4} ያም በዓረቦች ልቦና ውስጥ ባሳፈነው የሐረምን እና የነዋሪዎቹን ክብር በማላቅ ከረሃብ መግቧቸው ከፍርሃትም ያዳናቸው ነው።

መልስ - ሱረቱል ማዑን እና ተፍሲሯ፦
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{ያንን በምርመራው የሚያስተባብለውን አየህን? (ዐወቅከውን?) 1 * ይህም ያ የቲምን በኀይል የሚገፈትረው፤ 2 * ድኻንም በማብላት ላይ የማያግባባው ሰው ነው። 3 * ለሚሰግዱ ወዮላቸው፤ 4 * ለእነዚያ እነርሱ ከስግደታቸው ዘንጊዎች ለኾኑት፤ (ሰጋጆች)። 5 * ለእነዚያ እነርሱ ይዩልኝ ባዮች ለሆኑት። 6 * የዕቃ ትውስትንም (ሰዎችን) የሚከለክሉ ለሆኑት (ወዮላቸው)። 7} [ሱረቱ አል'ማዑን 1-7]
ተፍሲር፡
1- {ያንን በምርመራው የሚያስተባብለውን አየህን? (ዐወቅከውን?) 1} የትንሣኤ ቀን ምንዳን ያስተባበለውን አወቅከውን?
2- {ይህም ያ የቲምን በኀይል የሚገፈትረው፤ 2} ያ ወላጅ አልባን ከጉዳዩ በኋይል የሚገፈትረው ነው።
3- {ድኻንም በማብላት ላይ የማያግባባው ሰው ነው። 3} ራሱንም ይሁን ሌሎች ድሆችን እንዲመግቡ አያነሳሳም።
4- {ለሚሰግዱ ወዮላቸው፤ 4} ጣፋትና ስቃይ ለሰጋጆች ሆነ።
5- {ለእነዚያ እነርሱ ከስግደታቸው ዘንጊዎች ለሆኑት፤ (ሰጋጆች)። 5} ለነዚያ ምንም ሳያሳስባቸው በሶላታቸው ለሚቀልዱት ሰጋጆች ሆነ።
6- {ለእነዚያ እነርሱ ይዩልኝ ባዮች ለሆኑት። 6} ለነዚያ ሰላታቸውና ሥራዎቻቸው ለይዩልኝ ይስሙልኝ ለሆኑ፤ ለአላህም ብለው ኢኽላሳቸውን ለማያጠሩ ሰዎች ሆነ።
7- {የዕቃ ትውስትንም (ሰዎችን) የሚከለክሉ ለሆኑት (ወዮላቸው)። 7} እናም ሌሎችን ቢረዱበት ምንም ጉዳት በማይደርስባቸው ጉዳይም ሌሎችን ከመርዳት የሚታቀቡ ለሆኑት ወዮላቸው።

መልስ - ሱረቱል ከውሠር እና ተፍሲሯ፦
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{እኛ በጣም ብዙ በጎ ነገሮችን ሰጠንህ። 1 * ስለዚህ ለጌታህ ስገድ፤ (በስሙ) ሰዋም። 2 * ጠይህ (የሚጠላህ) እርሱ በእርግጥ (ዘሩ) የተቆረጠው ነው። 3 [ሱረቱል ከውሠር፡ 1-3]
ተፍሲር፡
1- {እኛ በጣም ብዙ በጎ ነገሮችን ሰጠንህ። 1} አንተ የአላህ መልዕክተኛው ሆይ! ብዙ መልካም ነገርን ሰጥተንሀል፤ ከነርሱም በጀነት ውስጥ ያለውን የአል-ከውሠር ወንዝ ይገኝበታል።
2- {ስለዚህ ለጌታህ ስገድ፤ (በስሙ) ሰዋም። 2} በመሆኑም በአሏህ የሚያጋሩ ሰዎች ከሚፈፅሙት ሺርክ በተፃራሪው አንተ ደግሞ እርድህንም ሶላትህንም ለርሱ ብቻ በማድረግ ለዚህ ችሮታው አላህን አመስግነው።
3- {ጠይህ (የሚጠላህ) እርሱ በእርግጥ (ዘሩ) የተቆረጠው ነው። 3} አንተን የሚጠላ ነው ከመልካም ነገር ሁሉ የተቆረጠና ቢወሳ እንኳ በክፋት ብቻ የሚወሳው።

መልስ - ሱረቱል ካፊሩን እና ተፍሲሯ፦
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{በላቸው «እናንተ ከሓዲዎች ሆይ! 1 * ያንን የምትግገዙትን (ጣዖት አሁን) አልግገዛም። 2 * እናንተም እኔ የምግገዛውን (አምላክም አሁን) ተገዢዎች አይደላችሁም። 3 * እኔም ያንን የተገዛችሁትን (ወደፊት) ተገዢ አይደለሁም። 4 * እናንተም እኔ የምግገዛውን (አምላክም አሁን) ተገዢዎች አይደላችሁም። 5 * ለእናንተ ሃይማኖታችሁ አልላችሁ። ለእኔም ሃይማኖቴ አለኝ። 6} [ሱረቱል ካፊሩን፡ 1-6]
ተፍሲር፡
1- {በላቸው «እናንተ ከሓዲዎች ሆይ! 1} የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! እንዲህ በላቸው፡ እናንተ በአላህ የካዳችሁ ከሀድያን ሆይ!
2- {«ያንን የምትግገዙትን (ጣዖት አሁን) አልግገዛም። 2} እኔ አሁንም ይሁን ለወደፊት የምታመልኩትን ጣዖታት የማመልክ አይደለሁም።
3- {«እናንተም እኔ የምግገዛውን (አምላክም አሁን) ተገዢዎች አይደላችሁም። 3} እናንተም እኔ የማመልከውን ይሀውም አላህ በብቸኝነት አታመልኩም።
4- {«እኔም ያንን የተገዛችሁትን (ወደፊት) ተገዢ አይደለሁም። 4} እኔም እናንተ የምታመልኳቸውን ጣዖታት አላመልክም።
5- {«እናንተም እኔ የምግገዛውን (አምላክም አሁን) ተገዢዎች አይደላችሁም። 3} እናንተም እኔ የማመልከውን አላህ በብቸኝነት አታመልኩም።
6- {«ለእናንተ ሃይማኖታችሁ አልላችሁ። ለእኔም ሃይማኖቴ አለኝ። 6} እናንተም ለራሳችሁ የፈለሰፋችሁት መጤ ሃይማኖት አላችሁ፤ እኔም አላህ ወደኔ ያወረደልኝ ሃይማኖቴ አለኝ።

መልስ - ሱረቱል ነስር እና ተፍሲሯ:
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{የአላህ እርዳታና (መካን) መክፈት በመጣ ጊዜ፤ 1 * ሰዎችንም ጭፍሮች እየሆኑ፤ በአላህ ሃይማኖት ውስጥ ሲገቡ ባየህ ጊዜ፤ 2 * ጌታህን ከማመስገን ጋር አጥራው። ምሕረትንም ለምነው። እርሱ ጸጸትን በጣም ተቀባይ ነውና። 3} [ሱረቱ አል'ነስር፡ 1-3]
ተፍሲር፡
1- {የአላህ እርዳታና (መካን) መክፈት በመጣ ጊዜ፤ 1} የአላህ መልዕክተኛ ሆይ! አላህ እርዳታውን ለግሷችሁ በሃይማኖታችሁ ድልን ባጎናፀፋችሁ፤ ሃይማኖቱንም በረዳና የመካ መከፈትም በተከስተ ጊዜ።
2- {ሰዎችንም ጭፍሮች እየሆኑ፤ በአላህ ሃይማኖት ውስጥ ሲገቡ ባየህ ጊዜ፤ 2} ሰዎችንም በቡድን በቡድን እየሆኑ ወደ እስልምና ሲገቡ ባየህ ጊዜ።
3- {ጌታህን ከማመስገን ጋር አጥራው። ምሕረትንም ለምነው። እርሱ ጸጸትን በጣም ተቀባይ ነውና። 3} የተላክህበት ተልዕኮ መጠናቀቁን የሚያሳይ ምልክት መሆኑን ተረድተህ ለዋለልህ የድል ፀጋ ምስጋና ለማቅረብ ጌታህን እያመሰገንከው ውዳሴን አቅርብ፤ እነሆ እርሱ የባሮቹን ንስሀ ተቀባይና ባሮቹንም ይቅር ባይ ነውና መሀርታውን ለምነው።

መልስ - ሱረቱል መሰድ እና ተፍሲሯ፦
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{የአቡ ለሀብ ሁለት እጆች ከሰሩ (ጠፉ፤ እርሱ) ከሰረም። 1 * ከእርሱ ገንዘቡና ያም ያፈራው ሁሉ ምንም አልጠቀመውም። 2 * የመንቀልቀል ባለቤት የሆነችን እሳት በእርግጥ ይገባል። 3 * ሚስቱም (ትገባለች)፤ እንጨት ተሸካሚ ስትሆን። 4 * በአንገትዋ ላይ ከጭረት የሆነ ገመድ ያለባት ስትሆን። 5} [ሱረቱ አል'መሰድ፡ 1-5]
ተፍሲር፡
1- {የአቡ ለሀብ ሁለት እጆች ከሰሩ (ጠፉ፤ እርሱ) ከሰረም። 1} የነብዩ ﷺ አጎት የሆነው አቡ ለሀብ ቢን ዐብዱል ሙጠሊብ ነብዩን ﷺ አዛ ሲያደርግ የነበረ በመሆኑ ስራው ኪሳራ ሆኖበት እጁ ከሰረ እንቅስቃሴውም ከንቱ ሆነ።
2- {ከእርሱ ገንዘቡና ያም ያፈራው ሁሉ ምንም አልጠቀመውም። 2} ገንዘቡ እና ልጁ እርሱን የጠቀሙት ምንድን ነው? ቅጣትን ከርሱ ሊያስቀሩለትም ሆነ እዝነትን ሊያመጡለት አልቻሉም።
3- {የመንቀልቀል ባለቤት የሆነችን እሳት በእርግጥ ይገባል። 3} በትንሳኤ ቀን ነበልባሏ አቃጣይ ወደ ሆነች እሳት ይገባታል።
4- {ሚስቱም (ትገባለች)፤ እንጨት ተሸካሚ ስትሆን። 4} ነብዩ ሶለሏሁ ዓለይሂ ወሰለምን በመንገዳቸው እሾህ እየጣለች የምታስቸግራቸው ሚስቱ ኡሙ ጀሚልም እንዲሁ ትገባታለች።
5- {በአንገትዋ ላይ ከጭረት የሆነ ገመድ ያለባት ስትሆን። 5} አንገቷ በተጠማዘዘ ገመድ ተቀፍድዳ ወደ ጀሀነም እሳት ትገባለች።

መልስ - ሱረቱል ኢኽላስ እና ተፍሲሯ፦
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{በል «እርሱ አላህ አንድ ነው። 1 * አሏህ (የሁሉ) መጠጊያ ነው። 2 * አልወለደም፤ አልተወለደምም። 3 * ለእርሱም አንድም ብጤ የለውም።» 4} [ሱረቱል ኢኽላስ፡ 1-4]
ተፍሲር፡
1- {በል «እርሱ አላህ አንድ ነው። 1} የአላህ መልእክተኛ ሆይ! እንዲህ በላቸው፡- እርሱ አላህ ነው፤ ከእርሱ በቀርም ሌላ አምላክ የለም።
2- {«አላህ (የሁሉ) መጠጊያ ነው። 2} ማለትም፡- የፍጥረታት ሁሉ ፍላጎት ወደ እርሱ ነው።
3- {«አልወለደም፤ አልተወለደምም። 3} ጥራት ይገባውና ለእርሱ ልጅም ወላጅም የለውም።
4- {«ለእርሱም አንድም ብጤ የለውም።»
4} ከፍጡራኑም ለርሱ ምንም አምሳያ የለውም።

መልስ - ሱረቱል ፈለቅ እና ተፍሲሯ፦
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{በል «በተፈልቃቂው ጎህ ጌታ እጠበቃለሁ። 1 * ከፈጠረው ፍጡር ሁሉ ክፋት። 2 * ከሌሊትም ክፋት ባጨለመ ጊዜ፤ 3 * በተቋጠሩ (ክሮች) ላይ ተፊዎች ከሆኑት (ደጋሚ) ሴቶችም ክፋት። 4 * ከምቀኛም ክፋት በተመቀኘ ጊዜ፤ (እጠበቃለሁ በል)።» 5} [ሱረቱ አልፈለቅ፡ 1-5]
ተፍሲር፡
1- {በል «በተፈልቃቂው ጎህ ጌታ እጠበቃለሁ። 1} ማለትም፡- አንተ መልእክተኛ -፡ እኔ የማለዳውን ጌታ አጥብቄ እይዛለሁ፤ ጥበቃውንም እሻለሁ።
2- {«ከፈጠረው ፍጡር ሁሉ ክፋት። 2} ፍጡራንን ከሚያስቸግር ክፋት ሁሉ።
3- {«ከሌሊትም ክፋት ባጨለመ ጊዜ፤ 3} በሌሊት ከሚጎሉ የአውሬዎችም የሌቦችም ክፋት ለመዳን አሏህን አጥብቄ እይዛለሁ።
4- {«በተቋጠሩ (ክሮች) ላይ ተፊዎች ከሆኑት (ደጋሚ) ሴቶችም ክፋት። 4} በቋጠሮ ላይ የሚተፉ ከሆኑት ሴት ደጋሚዎችም ክፋት ለመዳን አላህን አጥብቄ እይዛለሁ።
5- {«ከምቀኛም ክፋት በተመቀኘ ጊዜ፤ (እጠበቃለሁ በል)።» 5} ሰዎችን በተመቀኘ ጊዜ አሏህ የሰጣቸው ፀጋ እንዲወገድባቸውና ክፋትም እንዲያገኛቸው ከሚመኝ ምቀኛም ለመዳን አላህን አጥብቄ እይዛለሁ፤ ጥበቃውንም እሻለሁ።

መልስ - ሱረቱ ን-ናስ እና ተፍሲሯ:
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
{በል «በሰዎች ፈጣሪ እጠበቃለሁ። 1 * የሰዎች ሁሉ ንጉሥ በሆነው። 2 * የሰዎች አምላክ በሆነው። 3 * ብቅ እልም ባይ ከሆነው ጎትጓች (ሰይጣን) ክፋት። 4 * ከዚያ በሰዎች ልቦች ውስጥ የሚጎተጉት ከሆነው። 5 * ከጋኔኖችም ከሰዎችም (ሰይጣናት እጠበቃለሁ በል)።» 6} [ሱረቱ አን-ናስ፡ 1-6]
ተፍሲር፡
1- {በል «በሰዎች ፈጣሪ እጠበቃለሁ። 1} አንተ የአሏህ መልዕክተኛ ሆይ! እንዲህ በላቸው፦ የሰዎችን ጌታ አጥብቄ እይዛለሁ፣ ጥበቃውንም እሻለሁ።
2- {«የሰዎች ሁሉ ንጉሥ በሆነው። 2} እንዳሻው ያደርጋቸዋል፤ ከእርሱም ሌላ ባለቤት የሌላቸው በሆነው።
3- {«የሰዎች አምላክ በሆነው። 3} በእውነት የሚያመልኩት አምላካቸው፤ ከእርሱም ውጭ ለነርሱ በእውነት የሚያመልኩት አምላክ የሌላቸው በሆነው።
4- {«ብቅ እልም ባይ ከሆነው ጎትጓች (ሰይጣን) ክፋት። 4} በሰዎች ላይ ሹክሹክታውን ከሚወረውር የሰይጣን ክፋት።
5- {«ከዚያ በሰዎች ልቦች ውስጥ የሚጎተጉት ከሆነው። 5} ሹክሹክታውን ወደ ሰዎች ልቦና ከሚወረውረው ሰይጣን ክፋት።
6- {«ከጋኔኖችም ከሰዎችም (ሰይጣናት እጠበቃለሁ በል)።» 6} ማለትም ጉትጎታው ሰውም ይሁን ጂኒ ከክፋቱ ለመዳን የሰዎችን ጌታ አጥብቄ እይዛለሁ፣ ጥበቃውንም እሻለሁ።